1 ቀትር ላይ አብርሃም በመምሬ ትልልቅ ዛፎች አቅራቢያ በምትገኘው ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለት፤
2 ቀና ብሎም ሲመለከት፣ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ፤ ወዲያውም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ፣ ፈጥኖ ወደ ሰዎቹ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም እጅ ነሣ።
3 አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ ባሪያህን አልፈህ አትሂድ፤
4 ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ እዚህም ከዛፉ ሥር ዐረፍ በሉ።
5 ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ፣ እህል ቀምሳችሁ ትበረቱ ዘንድ ምግብ ላቅርብላችሁና ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ።”እነርሱም፣ “መልካም፤ እንዳልኸው አድርግ” አሉት።
6 አብርሃም በፍጥነት ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ ገብቶ፣ “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ስልቅ ዱቄት አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት።