13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች?
14 ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት በተባለው ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።”
15 ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች።እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት።
16 ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቊልቊል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ወጣ።
17 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን?
18 አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ።
19 ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።”