27 አብርሃም በማግስቱ፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሞ ወደነበረበት ቦታ ሄደ።
28 ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቊልቊል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ።
29 እንደዚህ አድርጐ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን አሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።
30 ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ አደረገ።
31 አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቶአል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ አብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም።
32 ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።”
33 በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።