ዘፍጥረት 19:29-35 NASV

29 እንደዚህ አድርጐ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን አሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።

30 ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ ውስጥ አደረገ።

31 አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቶአል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ አብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም።

32 ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።”

33 በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።

34 በማግስቱም ታላቂቱ ልጅ ታናሺቱን፣ “እኔ ትናንትና ማታ ከአባቴ ጋር ተኝቻለሁ፤ ዛሬም እንደ ገና የወይን ጠጅ እናጠጣው፤ አንቺም ደግሞ ከእርሱ ዘንድ ገብተሽ ተኚ፤ በዚህም የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ከአባታችን ዘር ማትረፍ እንችላለን” አለቻት።

35 በዚያችም ምሽት ደግሞ አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ትንሿ ልጁም ሄዳ ከአባቷ ጋር ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር።