ዘፍጥረት 2:19-25 NASV

19 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ።

20 ስለዚህ አዳም ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው።ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር።

21 እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንት ወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው።

22 እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።

23 አዳምም እንዲህ አለ፤“እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ሥጋም ከሥጋዬ ናት።ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።”

24 ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።

25 አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።