1 እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት።
2 ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት።
3 አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይስሐቅ አለው።
4 አብርሃም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባዘዘው መሠረት ልጁን ይስሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው።
5 አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ።
6 ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች።
7 ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።