ዘፍጥረት 24:12-18 NASV

12 ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጒዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው፤

13 እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ።

14 እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”

15 እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች።

16 ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች።

17 አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።

18 እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው።