ዘፍጥረት 24:2-8 NASV

2 አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤

3 ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋር እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ማልልኝ።

4 ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።”

5 አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው።

6 አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤

7 ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ።

8 ሴቲቱ አብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው።