ዘፍጥረት 25:17-23 NASV

17 እስማኤል በጠቅላላው መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

18 ዘሮቹም መኖሪያቸውን ከግብፅ ድንበር አጠገብ፣ ወደ አሦር በሚወስደው መንገድ፣ በኤውላጥና በሱር መካከል አደረጉ፤ ከወንድሞቻቸውም ሁሉ ጋር በጠላትነት ኖሩ።

19 የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድ ይህ ነው፤አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤

20 ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ርብቃ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ የሚኖረው የሶርያዊው የባቱኤል ልጅ፣ የሶርያዊውም የላባ እኅት ነበረች።

21 ይስሐቅ፣ ርብቃ መካን ስለ ነበረች ስለ እርሷ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ጸሎቱን ሰማ፤ ርብቃም ፀነሰች።

22 ልጆቹም በማሕፀኗ ውስጥ እርስ በርሳቸው ይጋፉ ጀመር፤ እርሷም “ለምን እንዲህ ይሆንብኛል?” ብላ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለመጠየቅ ሄደች።

23 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤“ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት።