ዘፍጥረት 29:3-9 NASV

3 መንጎቹ ሁሉ በጒድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጒድጓዱን አፍ ይገጥሙታል።

4 ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት።

5 እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው።እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት።

6 ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው።እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት።

7 ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው።

8 እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጒድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በስተቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ።

9 ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች።