2 የላባ አመለካከት ከቀድሞው የተለወጠበት መሆኑንም ያዕቆብ ተረዳ።
3 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህና ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።
4 ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤
5 እንዲህም አላቸው፤ አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) አልተለየኝም፤
6 መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም።
7 አባታችሁ ደሞዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጎዳኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አልፈቀደለትም።
8 እርሱ፣ ‘ደሞዝህ ዝንጒርጒሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደሞዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤