6 ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ።
7 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም፣ የያቆብን ልጅ ስለደፈረ ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ።
8 ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልቡ በልጃችሁ ፍቅር ተነድፎአል፤ እባካችሁ እንዲያገባት ፍቀዱለት።
9 በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችሁን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ።
10 አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።”
11 ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤
12 ጥሎሽ ብትሉኝ ጥሎሽ፣ ስጦታ ብትሉም የፈለጋችሁትን ያህል እሰጣለሁ፣ ብቻ ልጂቱን እንዳገባ ፍቀዱልኝ።”