2 ዔሳው ከከነዓን ሴቶች አገባ፤ እነርሱም፦ የኬጢያዊው የዔሎን ልጅ ዓዳን፣ የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳት አህሊባማ፣
3 እንዲሁም የነባዮት እኅት የሆነችው የእስማኤል ልጅ ቤሴሞት ነበሩ።
4 ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደችለት፤ ቤሴሞት ደግሞ ራጉኤልን ወለደችለት።
5 እንደዚሁም አህሊባማ የዑስን፣ የዕላምንና ቆሬን ወለደችለት፤ እነዚህ ዔሳው በከነዓን አገር የወለዳቸው ልጆች ናቸው።
6 ዔሳው ሚስቶቹን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ ቤተ ሰቦቹን በሙሉ እንደዚሁም የቀንድ ከብቶቹንና ሌሎቹንም እንሰሳት ሁሉ በከነዓን ምድር ያፈራው ሀብት እንዳለ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ።
7 ብዙ ሀብት ስለ ነበራቸው አብረው መኖር አልቻሉም፤ የነበሩበትም ስፍራ ከከብቶቻቸው ብዛት የተነሣ ሊበቃቸው አልቻለም።
8 ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው መኖሪያውን በተራራማው አገር በሴይር አደረገ።