16 ቃየንም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተ ምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ።
17 ቃየን ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ሄኖክን ወለደች። ቃየን የቈረቈረውን ከተማ በልጁ ስም ሄኖክ ብሎ ጠራው።
18 ሄኖክ ኢራድን ወለደ፤ ኢራድም መሑያኤልን፣ መሑያኤልም ማቱሣኤልን፣ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ።
19 ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ጺላ ነበር።
20 ዓዳ ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ከብት አርቢዎች አባት ነበረ።
21 ወንድሙም ዩባል ይባላል፤ እርሱም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበረ።
22 ሴላም ደግሞ ቱባልቃይን የተባለ ወንድ ልጅ ነበራት፤ እርሱም ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ ነበር። የቱባልቃይን እኅት ናዕማ ትባል ነበር።