5 ታስረው የነበሩት የግብፅ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው።
6 በማግስቱ ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው።
7 ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት አብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው።
8 እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጒምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት።ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
9 ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤
10 ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈቊጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ።
11 የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።”