ዘፍጥረት 41:4-10 NASV

4 እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።

5 ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ።

6 ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ።

7 የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር።

8 በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጒምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።

9 በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ።

10 በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር።