3 ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ወረዱ።
4 ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፣ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋር አላከውም።
5 ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ።
6 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፣ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት።
7 ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፣ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቍጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፣ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት።
8 ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም።
9 በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።