ዘፍጥረት 43:22-28 NASV

22 አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት።

23 የቤቱ አዛዥም፣ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ (ኤሎሂም) ነው፤ እኔ እንደሆንኩ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው።

24 የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው።

25 ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።

26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።

27 ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው።

28 እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው’። በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት።