5 መርከበኞቹ ሁሉ ፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱም ክብደት እንዲቀል፣ በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕሩ ጣሉት።ዮናስ ግን ወደ መርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ ተኛ፤ በከባድም እንቅልፍ ላይ ነበር።
6 የመርከቢቱም አዛዥ ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥና አምላክህን ጥራ እንጂ፤ ምናልባትም ያስበንና ከጥፋት ያድነን ይሆናል” አለው።
7 ከዚያም መርከበኞቹ እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደ መጣብን ለማወቅ፣ ኑ፣ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።
8 ከዚያም፣ “ይህ ሁሉ አስጨናቂ ነገር በማን ምክንያት እንደ መጣብን ንገረን፤ ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ የት ነው? ከየትኛውስ ሕዝብ ነህ?” አሉት።
9 እርሱም፣ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ የብስንና ባሕርን የፈጠረውን፣ የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” አለ።
10 እርሱ አስቀድሞ ነግሮአቸው ስለ ነበር፣ ከእግዚአብሔር እንደ ኰበለለ ዐወቁ፣ ስለዚህም በሁኔታው በመደንገጥ፣ “ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?” አሉት።
11 የባሕሩም ማዕበል እጅግ እየበረታ ስለሄደ፣ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት።