1 የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤
2 “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።”
3 ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ። በዚህ ጊዜ ነነዌ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ እርሷንም ከዳር እስከ ዳር ለመጐብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር።
4 ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ።
5 የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።