ዳንኤል 7:1-7 NASV

1 የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም አለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው።

2 ዳንኤል እንዲህ አለ፤ “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባሕር ሲያናውጡት ሌሊት በራእይ አየሁ፤

3 እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ።

4 “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነ ቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።

5 “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሎአል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ።

6 “ከዚያ በኋላ ተመለከትሁ፤ በፊቴ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤ በጀርባውም በኩል የወፍ ክንፍ የሚመስሉ አራት ክንፎች ነበሩት፤ ይህ አውሬ አራት ራስ ነበረው፤ ለመግዛትም ሥልጣን ተሰጠው።

7 “ከዚህ በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ በፊቴም የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ የሆነ አራተኛ አውሬ ነበር፤ ትልልቅ የብረት ጥርሶች ነበሩት፤ ያደቅና ይበላ፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር። ከእርሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን፣ ዐሥር ቀንዶች ነበሩት።