4 ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኀይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባ ባል የጥበብ ቃል አልነበረም፤
5 ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።
6 በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም።
7 ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው።
8 ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር።
9 ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣“ዐይን ያላየውን፣ጆሮ ያልሰማውን፣የሰውም ልብ ያላሰበውን፣እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል፤”
10 እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል።መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።