1 ተሰሎንቄ 1:3-9 NASV

3 ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።

4 በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እርሱ እንደ መረጣችሁ እናውቃለን፤

5 ምክንያቱም ወንጌላችን ወደ እናንተ የመጣው በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙም መረዳት እንጂ በቃል ብቻ አይደለም። ደግሞ ስለ እናንተ ስንል በመካከላችሁ እንዴት እንደኖርን ታውቃላችሁ።

6 እናንተ እኛንና ጌታን መስላችኋል፤ ምንም እንኳ ብርቱ መከራ ቢደርስባችሁም ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ተቀብላችኋል።

7 ከዚህም የተነሣ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙ ምእመናን መልካም ምሳሌ ሆናችኋል።

8 የጌታ ቃል ከእናንተ ወጥቶ በመቄዶንያና በአካይያ መሰማቱ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነት በሁሉ ቦታ ታውቆአል፤ ስለዚህ እኛ በዚህ ጒዳይ ላይ ምንም መናገር አያስፈልገንም፤

9 በእንዴት ያለ አቀባበል እንደ ተቀበላችሁንና ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነርሱ ራሳቸው ይናገራሉ፤