1 ዮሐንስ 4:1-7 NASV

1 ወዳጆች ሆይ፤ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።

2 የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚቀበል መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤

3 ኢየሱስን የማይቀበል መንፈስ ግን ከእግዚአብሔር አይደለም፤ እንደሚመጣ የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።

4 ልጆች ሆይ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ፤ እነርሱንም አሸንፋችኋቸዋል፤ ምክንያቱም በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል።

5 እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ የሚናገሩት እንደ ዓለም ነው፤ ዓለምም ይሰማቸዋል።

6 እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም፤ በዚህም የእውነትን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ እናውቃለን።

7 ወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንዋደድ፤ የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል።