ሐዋርያት ሥራ 1:12-18 NASV

12 ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ይህም ተራራ ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል ይርቅ ነበር።

13 ወደ ከተማዪቱም በገቡ ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፤ እነዚህም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብ፣ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ ቶማስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናኢ የተባለው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ።

14 እነዚህ ሁሉ ከሴቶቹና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ጋር እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋር በአንድ ልብ ሆነው ያለ ማቋረጥ ተግተው ይጸልዩ ነበር።

15 በእነዚያም ቀናት፣ ጴጥሮስ መቶ ሃያ በሚሆኑ ወንድሞች መካከል ቆሞ፣

16 እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፣ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፉ ቃል መፈጸም ስላለበት፣

17 እርሱ ከእኛ እንደ አንዱ ተቈጥሮ በዚህ አገልግሎት የመሳተፍ ዕድል አግኝቶ ነበር።”

18 ይህ ሰው ስለ ክፉ ሥራው በተከፈለው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በዚያም በግንባሩ ተደፍቶ ሰውነቱ እመካከሉ ላይ ፈነዳ፤ ሆድ ዕቃውም ተዘረገፈ፤