ሐዋርያት ሥራ 12:10-16 NASV

10 የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ ዐልፈው ወደ ከተማዪቱ በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለው የብረት መዝጊያ ዘንድ ደረሱ። መዝጊያውም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ሄዱ፤ አንዲት ስላች መንገድ እንዳለፉም ወዲያው መልአኩ ተለየው።

11 ጴጥሮስም ሲረጋጋ፣ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ።

12 ይህን ከተረዳ በኋላም፣ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአንድነት ወደሚጸልዩበት፣ ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ።

13 እዚያ ደርሶ የውጭውን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ማን እንደሆነ ለማጣራት ወደ በሩ ሄደች።

14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ፣ በጣም ከመደሰቷ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ በመመለስ፣ ጴጥሮስ በሩ ላይ ቆሞ እንደሚገኝ ተናገረች።

15 ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የእርሱ መልአክ ነው” አሉ።

16 ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።