ሐዋርያት ሥራ 17:4-10 NASV

4 አይሁድም አንዳንዶቹ የሰሙትን በመቀበል ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ ደግሞም ቍጥራቸው ብዙ የሆነ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግሪኮችና አያሌ ዕውቅ ሴቶች የሰሙትን ተቀብለው ከእነርሱ ጋር ተባበሩ።

5 አይሁድ ግን ስለቀኑ ወስላቶችን ከገበያ ቦታ አሰባሰቡ፤ ሕዝቡንም አነሣሥተው በከተማው ውስጥ ሁከት ፈጠሩ፤ ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ሕዝቡ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢያሶን ቤት እየተጣደፉ ሄዱ፤

6 ነገር ግን ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን በከተማው ባለ ሥልጣናት ፊት እየጐተቷቸው እንዲህ እያሉ ጮኹ፤ “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤

7 ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።”

8 ሕዝቡና የከተማውም ሹማምት ይህን በሰሙ ጊዜ ተሸበሩ፤

9 ከዚያም ኢያሶንንና ሌሎቹን በዋስ ለቀቋቸው።

10 ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፤ እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ።