16 ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቁታቸውን ሸሹ።
17 ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ።
18 ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ ተናዘዙ፤
19 ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ አምሳ ሺህ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ።
20 በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
21 ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ።
22 ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።