9 ፊስጦስም ለአይሁድ በጎ ለመዋል ፈልጎ፣ ጳውሎስን “ስለዚህ ጒዳይ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ በእኔ ፊት ለመፋረድ ፈቃደኛ ነህን?” አለው።
10 ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “አሁንም ቢሆን ፍትሕ ማግኘት በምችልበት፣ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ አንተ ራስህ በሚገባ እንደምታውቀው በአይሁድ ላይ ምንም በደል አልፈጸምሁም፤
11 ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ በደል ከተገኘብኝ፣ አልሙት አልልም፤ እነዚህ አይሁድ የሚያቀርቡብኝ ክስ እውነት ካልሆነ ግን፣ እኔን ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል የለም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ።”
12 ፊስጦስ ከመማክርቱ ጋር ከተመካከረ በኋላ፣ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልህ፣ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” አለው።
13 ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤
14 በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጒዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤
15 ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከሰውት ነበር።