30 “ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በሚነድ ቍጥቋጦ ነበልባል ውስጥ መልአክ ተገለጠለት።
31 ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤
32 ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም።
33 “ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የእግርህን ጫማ አውልቅ፤ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና።
34 በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ መልሼ እልክሃለሁ።’
35 “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘ገዥና ፈራጅ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህንን ሙሴ እግዚአብሔር በቊጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው።
36 እርሱም መርቶ ከግብፅ አወጣቸው፤ በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።