ማቴዎስ 19:8-14 NASV

8 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤

9 እላችኋለሁ፤ በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፣ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

10 ደቀ መዛሙርቱም፣ “የባልና የሚስት ጒዳይ እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል” አሉት።

11 ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ከተሰጣቸው በስተቀር ይህንን ትምህርት ማንም ሊቀበል አይችልም፤

12 ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”

13 ከዚያም እጆቹን በላያቸው ላይ ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አቀረቧቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡትን ሰዎች ገሠጿቸው።

14 ኢየሱስም፣ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማይ እንደ እነርሱ ላሉት ናትና” አላቸው።