7 ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም።
8 ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት።
9 ከወገን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ የመጡ ሰዎች ሬሳቸውን ሦስት ቀን ተኩል ይመለከታሉ፤ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ።
10 እነዚህ ሁለት ነቢያት የምድር ነዋሪዎችን ያሠቃዩ ስለ ነበር፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ በደረሰው ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይለዋወጣሉ።
11 ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው።
12 ከዚያም፣ “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።
13 በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማዪቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ፤ በነውጡም ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ የተረፉትንም ፍርሀት ያዛቸው፤ ለሰማይም አምላክ ክብር ሰጡ።