ራእይ 17:12-18 NASV

12 “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ፣ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ።

13 አንድ ሐሳብም አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፤

14 እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው ድል ይነሣሉ።”

15 መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራዪቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሆች፦ ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ናቸው።

16 አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቍቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል።

17 የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን እንዲፈጽሙ፣ ደግሞም በአንድ ሐሳብ እንዲስ ማሙና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነውና።

18 ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።