ራእይ 19:9-15 NASV

9 መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ።

10 እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።

11 ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።

12 ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከእርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በእርሱ ላይ ተጽፎአል።

13 እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሶአል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

14 የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።

15 ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ፤ “በብረት በትርም ይገዛቸዋል።” እርሱም ሁሉን ቻይ የሆነውን የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣ ወይን መጭመቂያ ይረግጣል።