ራእይ 2:5-11 NASV

5 እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ አስብ፤ ንስሓ ገብተህ ቀድሞ ታደርገው የነበረውን ነገር አድርግ፤ ንስሓ ካልገባህ፣ መጥቼ መቅረዝህን ከቦታው እወስድብሃለሁ።

6 ነገር ግን ይህ በጎ ነገር አለህ፤ እኔ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ አንተም ጠልተሃል።

7 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን፣ ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል ለሚነሣ በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ አደርገዋለሁ።

8 “በሰምርኔስ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣ ሞቶም የነበረውና ሕያው የሆነው እንዲህ ይላል፤

9 መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን እያሉ ስምህን የሚያጠፉትን ዐውቃለሁ፤ እነርሱ ግን የሰይጣን ማኅበር ናቸው።

10 ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ። እነሆ፤ ዲያብሎስ ሊፈትናችሁ አንዳንዶቻችሁን ወደ እስር ቤት ይጥላል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ ታማኝሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።

11 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል የሚነሣም በሁለተኛው ሞት ከቶ አይጐዳም።