1 ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤
2 ወንዙም በከተማዪቱ አውራ መንገድ መካከል ይፈስ ነበር። በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው ነበሩ።
3 ከእንግዲህ ወዲህ ርግማን ከቶ አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማዪቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል፤
4 ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በግምባራቸው ላይ ይሆናል።
5 ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።
6 መልአኩም፣ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኞች ናቸው። የነቢያት መናፍስት ጌታ አምላክ በቅርብ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ መልአኩን ልኮአል” አለኝ።