1 አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀውን ኮከብ አየሁ፤ ኮከቡም የጥልቁ ጒድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።
2 ጥልቁን ጒድጓድ በከፈተውም ጊዜ፣ ከውስጡ ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ያለ ጢስ ወጣ። ከጒድጓዱም በወጣው ጢስ ፀሓይና ሰማይ ጨለሙ።
3 ከጢሱም አንበጦች ወጥተው በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው።
4 እነርሱም የምድርን ሣር ወይም ማናቸውንም የለመለመ ተክል ወይም ዛፍ እንዳይጐዱ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ እንዲጐዱ ተነገራቸው፤