ራእይ 9:3-9 NASV

3 ከጢሱም አንበጦች ወጥተው በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው።

4 እነርሱም የምድርን ሣር ወይም ማናቸውንም የለመለመ ተክል ወይም ዛፍ እንዳይጐዱ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ እንዲጐዱ ተነገራቸው፤

5 እነርሱንም አምስት ወር ብቻ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሏቸው ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ የሚሠቃዩትም ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ሥቃይ ነው።

6 በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል።

7 አንበጦቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ደፍተዋል፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤

8 ጠጒራቸው የሴት ጠጒር፣ ጥርሳቸውም የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር።

9 የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት የሚገሠግሡ የብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ድምፅ ይመስል ነበር።