ቲቶ 2 NASV

1 አንተ ግን ከትክክለኛው ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውን አስተምር።

2 አረጋውያን ጭምቶች፣ የተከበሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙና በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥት ጤናማነት ያላቸው እንዲሆኑ ምከራቸው።

3 እንዲሁም አሮጊቶች በአኗኗራቸው የተከበሩ እንዲሆኑ፣ በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉ ወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ እንዳይሆኑ አስተምራቸው፤

4 እንዲህ ከሆኑ፣ ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ ማስተማር ይችላሉ፤

5 የእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ ራሳቸውን የሚገዙና ንጹሓን፣ በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮች፣ ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑ ያስተምሯቸው።

6 እንዲሁም ወጣት ወንዶች ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው።

7 በማንኛውም ነገር መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ ራስህን አርኣያ አድርገህ አቅርብላቸው። በምታስ ተምራቸውም ትምህርት ጭምተኛነትን፣ ቁም ነገረኛነትን፣

8 የማይነቀፍ ጤናማ አነጋገር አሳይ፤ ይኸውም ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር ነው።

9 ባሮች ለጌቶቻቸው በማንኛውም ነገር እንዲገዙ፣ ደስ እንዲያሰኟቸው፣ የአጸፋ ቃል እንዳይመልሱላቸው አስተምር፤

10 አይስረቁ፤ ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው።

11 ድነት የሚገኝበት የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና፤

12 ይህም ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛት በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር ያስተምረናል፤

13 ይህም የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ ነው፤

14 እርሱም ከክፋት ሊቤዠን መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋውን የእርሱ የሆነውን ሕዝብ ለራሱ ያነጻ ዘንድ ራሱን ስለ እኛ ሰጥቶአል።

15 እንግዲህ ልታስተምር የሚገባህ እነዚህን ነው፤ በሙሉ ሥልጣን ምከር፤ ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።

ምዕራፎች

1 2 3