2 ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች። የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር።
3 ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ።
4 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ።
5 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።
6 እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ።
7 ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ።
8 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።