2 ከዚያም የአባቱ የእስራኤል ሬሳ እንዳይፈርስ ባለ መድኀኒት የሆኑ አገልጋዮቹ በመድኀኒት እንዲቀቡት አዘዘ። ባለ መድኀኒቶቹም እንዳይፈርስ ሬሳውን፣ በመድኀኒት ቀቡት።
3 ሬሳው እንዳይፈርስ መድኀኒት መቀባቱ በአገሩ ልማድ መሠረት አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ግብፃውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት።
4 የሐዘኑ ጊዜ እንዳበቃ ዮሴፍ የፈርዖንን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በፊታችሁ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩልኝ፣
5 ‘የምሞትበት ጊዜ ስለ ተቃረበ፣ በከነዓን ምድር ራሴ ቈፍሬ ባዘጋጀሁት መቃብር እንድትቀብረኝ’ ሲል አባቴ አስምሎኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ልቅበር ከዚያም እመለሳለሁ።”
6 ፈርዖንም፣ “ባስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው።
7 ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ወጣ፤ የፈርዖን ሹማምት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የግብፅ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት።
8 እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ አብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ።