16 ዮአስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
17 የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
18 በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
19 አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሴራ ስለጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ላኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉት ሰዎች ወደዚያው ልከው አስገደሉት፤
20 ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ መጥቶ በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።
21 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።
22 አሜስያስ ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር።