2 ነገሥት 6 NASV

መጥረቢያው ተንሳፈፈ

1 የነቢያት ማኅበር ኤልሳዕን እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፣ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠቦናል፤

2 ስለዚህ ወደ ዮርዳኖስ ሄደን፣ እያንዳንዳችን ምሰሶ ቈርጠን እናምጣ፣ በዚያም የምንቀመጥበትን መኖሪያ እንሥራ።”እርሱም፣ “ይሁን ሂዱ” አላቸው።

3 ከመካከላቸውም አንዱ፣ “አንተስ ከአገልጋዮችህ ጋር አትመጣምን?” አለው።ኤልሳዕም፣ “እሺ እሄዳለሁ” አለ፤

4 አብሮአቸውም ሄደ። ወደ ዮርዳኖስም ሄደው ዛፎች መቊረጥ ጀመሩ።

5 ከእነርሱም አንዱ ዛፍ እየቈረጠ ሳለ፣ መጥረቢያው በሮ ከውሃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም፣ “አየ ጒድ ጌታዬ፤ የተውሶ መጥረቢያ እኮ ነው!” ብሎ ጮኸ።

6 የእግዚአብሔርም ሰው፣ “በየት በኩል ነው የወደቀው?” ሲል ጠየቀ። ቦታውን ባሳየውም ጊዜ ኤልሳዕ እንጨት ቈርጦ ወደ ውሃው ውስጥ በመጣል መጥረቢያውን እንዲንሳፈፍ አደረገው።

7 ከዚያም፣ “በል አውጣና ውሰደው” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘርግቶ ወሰደው።

ኤልሳዕ ሶርያውያንን አሳወረ

8 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከጦር አለቆቹ ጋር ከተመካከረ በኋላም፣ “በዚህ፣ በዚህ ቦታ እሰፍራለሁ” አለ።

9 የእግዚአብሔርም ሰው፣ “ሶርያውያን በዚያ ታች ወርደዋልና በዚያ በኩል እንዳታልፍ ተጠንቀቅ” ሲል ለእስራኤል ንጉሥ ላከበት።

10 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው የነገረውን ቦታ አስቃኘ፤ ኤልሳዕም ንጉሡን እንደዚህ ካሉት ቦታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ከአንድ ሁለት ጊዜ በላይ አስጠነቀቀው።

11 ይህም የሶርያን ንጉሥ እጅግ ስላበሳ ጨው፣ የጦር አለቆቹን ጠርቶ፣ “ከመካከላችን ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ ለምን አትነግሩኝም?” ሲል ጠየቃቸው።

12 ከጦር አለቆቹም አንዱ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ከእኛ በኩል ማንም ሰው የለም፤ ነገር ግን አንተ በእልፍኝህ ሆነህ እንኳ የምትናገረውን አንዲቱም ሳትቀር ለእስራኤል ንጉሥ የሚነግረው በእስራኤል ያለው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው” አለው።

13 ንጉሡም፣ “ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው፣ የት እንደሚገኝ ፈልጉ” ሲል አዘዘ። ከዚያም፣ “በዶታይን ይገኛል” የሚል ዜና ደረሰው።

14 ስለዚህ ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት ወደዚያ ላከ። እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ።

15 የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16 ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17 ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

18 ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19 ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

20 ወደ ከተማዪቱም ከገቡ በኋላ ኤልሳዕ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲያዩ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ክፈት” አለ። እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ከፈተ። እነርሱም በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።

21 የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።

22 እርሱም፣ “አትግደላቸው፤ ለመሆኑ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸውን ትገድላቸው ዘንድ ይገባሃልን? አሁንም የሚበሉትንና የሚጠጡትን አስቀርብላቸው፤ በልተው ጠጥተውም ወደ ጌታቸውም ይሂዱ” አለው።

23 ስለዚህ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ አሰናብቶአቸው ወደ ጌታቸው ሄዱ። የሶርያ አደጋ ጣዮችም የእስራኤልን ምድር ለመውረር ከዚያ በኋላ አልተመለሱም።

በተከበበችው ሰማርያ የተከሠተ ራብ

24 ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሐዳድ ሰራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት።

25 ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማኒያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በአምስት ሰቅል ብር እስኪ ሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።

26 የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ጌታዬ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እባክህ ርዳኝ!” አለች።

27 ንጉሡም፣ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከዐውድማው ነው ወይስ ከወይን መጥመቂያው የምረዳሽ?” ሲል መለሰላት።

28 ከዚያም፣ “ለመሆኑ ችግርሽ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃት።እርሷም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ይህች ሴት፣ ‘ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪው፤ ነገ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላዋለን’ አለችኝ።

29 ስለዚህ ልጄን ቀቅለን በላነው። በማግሥቱም፣ ‘እንድንበላው ልጅሽን አምጪው’ አልኋት፤ እርሷ ግን ደበቀችው።”

30 ንጉሡም ሴቲቱ ያለችውን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥሩ ላይ በሚመላለስበትም ጊዜ በውስጥ ማቅ መልበሱን ሕዝቡ አየ።

31 ንጉሡም፣ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በዐንገቱ ላይ ካደረ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ዛተ።

32 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በቤቱ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎችም አብረውት ተቀምጠው ነበር። ንጉሡም መልእክተኛ ቀድሞት እንዲሄድ አደረገ። የተላከውም ሰው ከመድረሱ በፊት ኤልሳዕ ለሽማግሌዎቹ፣ “ይህ ነፍሰ ገዳይ ራሴን ለመቊረጥ ሰው መላኩን ታያላችሁ? እነሆ፤ አሁንም መልእክተኛው ሲደርስ በሩን ዘግታችሁ እንዳይገባ አድርጉ። የጌታው የእግሩ ኮቴ ከኋላው ይሰማ የለምን?” አላቸው።

33 ኤልሳዕ ከሽማግሌዎቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለም፣ መልእክተኛው ወደ እርሱ ወረደ። ንጉሡም ደርሶ፣ “ይህ ጥፋት የመጣው ከእግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እኔ ከእግዚአብሔር ምን እጠብቃለሁ?” አለ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25