1 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ገበረለት፤ ከዚያ በኋላ ግን ሐሳቡን ለውጦ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ።
2 እግዚአብሔርም በኢዮአቄም ላይ ባቢሎናውያን፣ ሶርያውያን፣ ሞዓባውያንና አሞናውያን አደጋ ጣዮችን ላከበት፤ በአገልጋዮቹ በነቢያቱ አማካይነት በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ይሁዳን ያጠፉ ዘንድ እነዚህን ላከ።
3 ከፊቱ ያርቃቸው ዘንድ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ በትክክል ሊፈጸሙ ችለዋል፤ ይህም ምናሴ ስለ ሠራው ኀጢአትና ስለ ፈጸመውም ሁሉ፣
4 እንዲሁም ንጹሕ ደም ስላፈሰሰ ነው። ኢየሩሳሌምም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ፤ እግዚአብሔር ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።
5 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
6 ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ዮአኪንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
7 የባቢሎንም ንጉሥ ከግብፅ ደረቅ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ የነበረውን ግዛቱን ሁሉ ወስዶበት ስለ ነበር፣ የግብፅ ንጉሥ ከአገሩ ዳግም ለዘመቻ አልወጣም።
8 ዮአኪን ሲነግሥ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሦስት ወር ገዛ። እናቱ ኔስታ ትባላለች፤ እርሷም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።
9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ጦር አለቆች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቧት፤
11 የጦር አለቆቹ ከበባ በሚያደርጉበትም ሰዓት ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ከተማዪቱ መጣ።
12 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፣ እናቱ፣ የክብር አጃቢዎቹ፣ መሳፍንቱና ሹማምቱ ሁሉ እጃቸውን ለባቢሎን ንጉሥ ሰጡ። የባቢሎን ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው።
13 እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ አጋዘ፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያሠራቸውንም የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ።
14 ደግሞም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዳለ የጦር አለቆቹንና ተዋጊዎቹን በሙሉ፣ የእጅ ባለሙያዎችንና ቀጥቃጮችን ሁሉ ጨምሮ ባጠቃላይ ዐሥር ሺህ ሰው በምርኮ ወደ አገሩ ወሰደ። በዚያ የቀሩት የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች ብቻ ነበሩ።
15 ናቡከደነፆር ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው እንዲሁም የንጉሡን እናት፣ ሚስቶቹን፣ ሹማምቱና በአገር የታወቁትን ታላላቅ ሰዎችም ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ወሰደ።
16 ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ በአጠቃላይ ብርቱ የሆኑትንና ለጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰባት ሺህ ተዋጊዎች አንድ ሺህ የእጅ ባለሙያዎችንና ቀጥቃጮችን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ።
17 ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያን በምትኩ አነገሠው፤ ስሙንም ሴዴቅያስ አለው።
18 ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
19 ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
20 እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቊጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አራቃቸው።በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።