2 ነገሥት 18 NASV

የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ

1 የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ።

2 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱ የዘካርያስ ልጅ ስትሆን ስሟ አብያ ይባል ነበር።

3 አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

4 በየኰረብታው ላይ ያሉትን ማምለኪያዎች አስወገደ፤ አዕማደ ጣዖታትን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ሙሴ የሠራውን የናስ እባብ፣ እስራኤላውያን እስከዚያች ጊዜ ድረስ ዕጣን ያጤሱለት ስለ ነበር ሰባበረው፤ ይህም ነሑሽታን ይባል ነበር።

5 ሕዝቅያስም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም።

6 ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ።

7 እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት። በአሦር ንጉሥ ላይ ዐመፀ፤ ግብር መገበሩንም ተወ።

8 እስከ ጋዛና እስከ ግዛቷ ዳርቻ በመዝለቅ ፍልስጤማውያንን ከመጠበቂያ ማማ እስከ ተመሸገችው ከተማ ድረስ ድል አደረጋቸው።

9 ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤

10 በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስ ራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር።

11 የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በሜዶን ከተሞች አሰፈራቸው።

12 ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም።

13 ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ አደጋ ጥሎ ያዛቸው።

14 ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው።

15 ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው።

16 በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው።

ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን አስፈራራ

17 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋር የይሁዳ ንጉሥ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ በመስኖ የሚወርድበትን ስፍራ ያዙ።

18 ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄደ።

19 የጦር መሪውም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤“ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ “ለመሆኑ እንዲህ የልብ ልብ እንድታገኝ ያደረገህ ምንድ ነው?

20 የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፣ ነገር ግን ወሬ ብቻ ነው። በእኔ ላይ እንዲህ ያመፅኸውስ በማን ተመክተህ ነው?

21 እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብፅ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው።

22 ደግሞም፣ “የምንመካው በአምላካችን በእግዚአብሔር ነው” የምትለኝ ከሆነም፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፣ “ማምለክ ያለባችሁ ኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ነው” ብሎ የኰረብታ ላይ መመለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰበት እርሱ አይደለምን?

23 “ ‘ከሆነልህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ውርርድ ግጠም፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ፣ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።

24 የምትመካው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ?

25 ከዚህም በቀር አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃል? በዚች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ”

26 ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ሳምናስና ዮአስ የጦር መሪውን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለ ምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት።

27 የጦር አዛዡም፣ “ለመሆኑ ጌታዬ ይህን እንድናገር የላከኝ፣ ለጌታችሁና ለእናንተ ብቻ ነውን? እነርሱም እንደ እናንተው ገና ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፣ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ጭምር አይደለምን?”

28 ከዚያም የጦር አዛዡ ቆሞ ድምፁን ከፍ በማድረግ በዕብራውያን ቋንቋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ!

29 ንጉሡ የሚለውም ይህ ነው፤ ‘ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ እንዳያታልላችሁ፤

30 ደግሞም ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ያድነናል፤ ይህችም ከተማ ለአሦር ንጉሥ አልፋ አትሰጥም’ በማለት በእግዚአብሔር እንድትታመኑ የሚነግራችሁን አትቀበሉ።” ’

31 “ሕዝቅያስንም አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋር ሰላም መሥርቱ፤ እጃችሁን ስጡ፤ ከዚያም ከእናንተ እያንዳንዱ ከገዛ ወይኑና ከገዛ በለሱ ይበላል፤ ከገዛ ጒድጓዱም ውሃ ይጠጣል፤

32 ይህም የሚሆነው የእናንተኑ ወደ ምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለበት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’“ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት።

33 ለመሆኑ ከአሕዛብ አማልክት ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ማን አለ?

34 የሐማትና የአርፋድ አማልክት እስቲ የት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?

35 ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእኔ ለማዳን የቻለ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊታደጋት እንዴት ይችላል?”

36 ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና።

37 ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ፤ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ ጸሓፊው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቅያስም መጥተው የጦር አዛዡ ያላቸውን ነገሩት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25