2 ነገሥት 15 NASV

የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ

1 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ።

2 ሲነግሥም ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

3 አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ ዓዛርያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

4 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና እጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

5 እግዚአብሔርም ንጉሡን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ በለምጽ መታው፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያን ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።

6 በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

7 ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ

8 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ።

9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

10 የያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

11 በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦአል።

12 በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ።

የእስራኤል ንጉሥ ሰሎም

13 የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በእስራኤል ላይ ነገሠ። በሰማርያ ተቀምጦ አንድ ወር ገዛ።

14 የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

15 በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

16 በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ።

የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም

17 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀም ጦም ዐሥር ዓመት ገዛ።

18 በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

19 ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌ ልሶርፀ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው።

20 ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም አምሳ፣ አምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ።

21 በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

22 ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ ፋቂስያስ

23 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።

24 ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25 ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ አምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋር ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ።

26 በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎአል።

የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ

27 የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በሰማርያ ከተማ፣ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሃያ ዓመትም ገዛ።

28 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

29 በእስራኤል ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካን፣ ያኖዋን፣ ቃዴስንና ሐጾርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ጭምር ያዘ። ሕዝቡንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰደው።

30 ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ አሤረበት፤ አደጋ ጥሎም ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመትም ሆሴዕ በፋቁሔ እግር ተተክቶ ነገሠ።

31 በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸማቸውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም

32 የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ።

33 ሲነግሥም ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፤ ኢየሩሳ ትባል ነበር።

34 አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።

35 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር መልሶ ሠራ።

36 በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

37 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔን ይሁዳን እንዲወጉ አደረገ።

38 ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ አባቶቹ በተቀበሩበትም፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25