2 ነገሥት 25 NASV

1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር መላ ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ፤ ከከተማዪቱ ቅጥር ውጭ ሰፈረ፤ ዙሪያውንም በሙሉ በዕርድ ከበባት።

2 ከተማዪቱም እስከ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች።

3 በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ውስጥ የተከሠተው ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚቀምሰው አጣ።

4 ምንም እንኳ ባቢሎናውያን ከተማዪቱን እንደ ከበቧት ቢሆንም የከተማዪቱ ቅጥር ተጣሰ፤ ሰራዊቱም ሁሉ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ባሉት በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በሚገኘው በር አልፎ በሌሊት ሸሸ፤ ሽሽቱም ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር።

5 ይሁን እንጂ የባቢሎን ሰራዊት ንጉሡን ተከታትሎ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ደረሰበት። ወታደሮቹ ሁሉ ተለይተውት ተበታትነው ነበር።

6 እርሱም ተያዘ፤ በዚያን ጊዜ ሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤ ቅጣትም ተፈረደበት።

7 ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየም የገዛ ልጆቹን ገደሉበት፤ ከዚያም ሁለት ዐይኖቹን በማውጣት በናስ ሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

8 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የክብር ዘቡ ሰራዊት አዛዥና የባቢሎን ንጉሥ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የሆነው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

9 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱንና በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ታላላቅ ሕንጻ ለእሳት ዳረገው።

10 በክብር ዘቡ አዛዥ የተመራው መላው የባቢሎን ሰራዊትም በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበረውን ቅጥር አፈረሰው።

11 የክብር ዘቡ አዛዥም በከተማዪቱ ቀርቶ የነበረውን፣ ከድቶም በዚያ የተገኘውን ሰው ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ የገባውን ጭምር በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው።

12 ሆኖም አዛዡ ከአገሬው ሰዎች ምንም የሌላቸውን ድኾች ወይን እንዲተክሉ፣ ዕርሻም እንዲያርሱ እዚያው ተዋቸው።

13 ባቢሎናውያን የናስ ዐምዶቹን፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ክብ በርሜል ሰባብረው ናሱን ወደ ባቢሎን ወሰዱ።

14 እንዲሁም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ጭልፋዎቹን፣ ባጠቃላይም ከናስ የተሠሩትን የቤተ መቅደሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ወሰዱ።

15 የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጽናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ።

16 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ የውሃ ማጠራቀሚያው ክብ በርሜልና ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎቹ ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር።

17 እያንዳንዱ ዐምድ ዐሥራ ስምንት ክንድ ሲሆን፣ የናስ ጒልላት ነበረው፤ የጒልላቱ ርዝመት ሦስት ክንድ ሆኖ፣ ዙሪያውን በሙሉ የናስ መርበብና የሮማን ፍሬዎች ቅርጽ ነበረው፤ ሌላውም ዐምድ ከነቅርጾቹ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

18 የክብር ዘብ አዛዡም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕረግ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው።

19 እስከዚያች ጊዜ ድረስ በከተማዪቱ ውስጥ ከቀሩትም የተዋጊዎቹን አለቃና አምስት የንጉሡን አማካሪዎች ወሰዳቸው። ደግሞም የአገሩን ሕዝብ ለውትድርና የሚመለምለውን ዋና የጦር አለቃ የነበረውን ጸሓፊውንና በከተማዪቱ ውስጥ የተገኙትን የጸሓፊውን ሥልሳ ሰዎች ወሰዳቸው።

20 አዛዡ ናቡዘረዳንም እነዚህን ሁሉ ይዞ ልብና ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።

21 ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር እዚያው ልብና ውስጥ አስገደላቸው። ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ።

22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የሳፋን የልጅ ልጅ የሆነውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን እዚያው በቀረው በይሁዳ ሕዝብ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።

23 መላው የሰራዊቱ ጦር አለቆችና ሰዎቻቸው የባቢሎን ንጉሥ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ጎዶልያስን መሾሙን ሲሰሙ፣ እርሱ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ እነርሱም የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋዊው የተን ሑሜት ልጅ ሠራያ የማዕካታዊው ልጅ ያእዛንያና ሰዎቻቸው ነበሩ።

24 ጎዶልያስም፣ “የባቢሎናውያንን ሹማምት አትፍሩ፤ እዚሁ አገር ኑሩ፤ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ ሁሉም ነገር ይሳካላችኋል” ሲል ይህንኑ በቃለ መሐላ አረጋገጠላቸው።

25 ነገር ግን በሰባተኛው ወር ንጉሣዊ ዝርያ የነበረው የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ዐሥር ሰዎች ይዞ መጥቶ ጎዶልያስንና በምጽጳ አብረውት የነበሩትን የይሁዳን ሰዎችና ባቢሎናውያንን ገደለ።

26 ባቢሎናውያንን ከመፍራታቸው የተነሣም ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሕዝቡ ሁሉ ከሰራዊቱ የጦር አለቆች ጋር ወደ ግብፅ ሸሹ።

ዮአኪን ከእስራት ተፈታ

27 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን ዮርማሮዴቅ በባቢሎን በነገሠ በዓመቱ ዮአኪንን ከእስራቱ ፈታው።

28 በርኅራኄም መንፈስ አነጋገረው፤ በባቢሎን አብረውት ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ያለውን የክብር ቦታ ሰጠው።

29 ዮአኪንም የእስር ቤት ልብሱን ጣለ፤ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማዕድ ዘወትር ይመገብ ጀመር፤

30 ንጉሡም ለዮአኪን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የዕለት ቀለቡን ይሰጠው ነበር።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25