1 አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ እጅግም ስላገነነው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ።
2 ከዚያም ሰሎሞን ለመላው እስራኤል፣ ለሻለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለዳኞች፣ ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንዲሁም ለየቤተ ሰቡ አለቆች ተናገረ።
3 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የአምላክ የመገናኛ ድንኳን በዚያ ስለ ነበር፣ ሰሎሞንና መላው ጉባኤ በገባዖን ወዳለው ኰረብታ ሄዱ።
4 በዚያ ጊዜ ዳዊት የአምላክን ታቦት ከቂሪያት ይዓሪም በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤
5 ይሁን እንጂ የሆር ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው መሠዊያ በገባዖን በእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ፊት ለፊት ይገኝ ነበር፤ ስለዚህ ሰሎሞንና ጉባኤው ይህንኑ ፈለጉ።
6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጥቶ በላዩ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7 በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ጠይቀኝ” አለው።