2 ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ።
3 ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ።
4 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ወሰነ።
5 ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦም፣ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በየዓመቱ ለማደስ ገንዘብ ከእስራኤል ሁሉ ሰብስቡ፤ ይህንንም አሁኑኑ አድርጉት” አላቸው። ሌዋውያኑ ግን ቸል አሉ።
6 ስለዚህ ንጉሡ ሊቀ ካህኑን ዮዳሄን ጠርቶ፣ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ጉባኤ ለምስክሩ ድንኳን እንዲወጣ የወሰኑትን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላተጋሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።
7 በዚህ ጊዜ የዚያች ክፉ የጎቶልያ ልጆች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰብረው በመግባት የተቀደሱ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ለበኣል ጣዖታት አገልግሎት እንዲውሉ አድርገው ነበር።
8 በንጉሡም ትእዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በር አጠገብ በውጭ በኩል አኖሩት።