11 ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”
12 ከዚያም እነዚሁ ሌዋውያን በሥራው ላይ ተሰማሩ፤ ከቀዓት ዘሮች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፤ከሜራሪ ዘሮች፣የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፤ከጌድሶን ዘሮች፣የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፤
13 ከኤሊጻፋን ዘሮች፣ሺምሪና ይዒኤል፤ከአሳፍ ዘሮች፣ዘካርያስና መታንያ፤
14 ከኤማን ዘሮች፣ይሒኤልና ሰሜኢ፣ከኤዶታም ዘሮች፣ሸማያና ዑዝኤል።
15 ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ፣ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቃል ተከትሎ ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማንጻት ገቡ።
16 ካህናቱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትንም ማናቸውንም የረከሰ ነገር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያኑም ተሸክመው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሉት።
17 ማንጻቱንም በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በዚያኑ ወር በስምንተኛው ቀን እስከ መቅደስ ሰበሰብ ደረሱ፤ በሚቀጥሉትም ስምንት ቀናት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ፤ የመቀደሱም ሥራ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።